APRIL 20, 2024 | BAY-AREA | JOINT CONFERENCE
The third of the five regional celebrations was held in the Bay-Area, CA on Saturday April 6, 2024.
የኢ.ወ.አ.ክ.ህ በሰሜን አሜሪካ የኢዮቤልዩ ጉዞ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ
ካሊፎርኒያ፡ በዚህ ዓመት ዋሺንግቶን ዲሲ የሚከበረውን የኢ.ወ.አ.ክ.ህ. በሰሜን አሜሪካ 50ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ በኤፕሪል 6 ህብረቱ በቤይኤሪያ አካባቢ ባዘጋጀው የመንፈሳዊ መነቃቂያ ኮንፈረንስ በሳክራሜንቶ፣ ሳንሆዜ፣ ኦክላንድ እና ሳንፍራንሲስኮ የሚገኙ ቤተክርስቲያናት ምእመናንና መሪዎች የተገኙበት በአይነቱ ልዩ የሆነ የአንድነት ጊዜ ፍሪሞንት በሚገኘው ፕሪንስ ኦፍ ፒስ ሉተራን ቤ/ክ እንደተከናወነ ተገለጸ።
ከ500 ሰዎች በላይ በተገኙበት በዚህ መርሃግብር የኢ.ወ.አ.ክ.በሰሜን አሜሪካ ዋና ዳይሬክተር ፓስተር ሰሎሞን ጥላሁን እና ፓስተር ሳምሶን ጥላሁን የእግዚአብሄርን ቃል ያቀረቡ ሲሆን በአካቢቢው ከሚገኙ ቤተክርስቲያናት የተውጣጡ የመዘምራን ቡድን በዝማሬ አገልግለዋል። በቦታው የተገኙ ቅዱሳን እንደገለጹት እያንዳንዱ የመርሃግብሩ አካል ቀልብ ሳቢ በሆነ መልኩ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነበር። በፓስተር መከተ አብዩ መሪነትም አማኞች የጌታን እራት በአንድነት እንዲወስዱ ተደርጓል።
የፕሮግራሙ አስተባባሪ እና የህብረቱ የቦርድ አባል ፓስተር ታሪኩ ስምኦን “የቤተክርቲያንን መልክ የሚመልስ፣ ገጽታዋን የሚያድስ፣ ወደ ፈውስ የሚያመጣና ተስፋዋን የሚያድስ እንዲሁም በመካከላችን የ አንድነት መንፈስ እንዲፈጠር ያደረገ ዕለት ነበር።” ብለዋል።
ለብዙ አመታት ተገናኝተው የማያውቁ ወገኖች እንዲገናኙ ምክንያት እንደሆነም አክለው ገልጸዋል። በሚዲያ አገልግሎት በስፋት የሚታወቀው ወንድም ተሻገር ገመቺስ በበኩሉ “ቀደም ባሉት አመታት የነበረው የክርስቲያኖችን ፍቅርና አንድነትን እንድናስታውስ ያደረገንና በሁላችንም ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የደስታን ስሜት የፈጠረ ነበር።” በማለት ተናግሯል። ወንድም ተሻገር አክሎ እንደገለጸው ምንም እንኳን ብዙ የተደከመበት ቢሆንም ውጤቱና የኮንፈረንሱ ይዘት ለአብዛኛዎቹ ከተጠበቀው በላይ ነበር።
ወጣቶች፣ የኮሌጅ ተማሪዎች እና ልጆች በቦታው የተገኙ ሲሆን ከመርሃግብሩ ፍጻሜ በኋላ ተመሳሳይ ስሜት እንደፈጠረባቸው ከታዳሚዎቹ መካከል ገልጸዋል።
የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች እንዳስረዱት የፕሮግራሙ መሳካት ምክንያት በእግዚአብሄር እርዳታ የፓስተሮች እንዲሁም የመሪዎች ከፍተኛ ትጋትና እርስ በርስ መተባበር ነበር። ተመሳሳይ መርሃግብሮች በተለያዩ የሰሜን አሜሪካ ክፍለግዛቶች እንደሚከናወኑ በዕለቱ ተገልጿል።
በታላቅ ናፍቆት የሚጠበቀው የወርቅ ኢዮቤልዩ ከሐምሌ 26 እስከ 27 በዋሽንግተን ዲሲ ኮንቬንሽን ሴንተር ከመላ አገሪቱ እና ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ወንጌላዊያን አማኞች በሚገኙበት ይከበራል። ከዚያ ቀደም ብሎ በተለያዩ አካባቢዎች ለታላቁ ኢዮቤልዩ የሚያዘጋጅ “ጉዞ ወደ ኢዮቤልዩ” በመባል የተሰየመው ቅድመ ከበራ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በመሆኑም መጀመሪያ የተካሄደው በሲንሲናቲ ከተማ በሶስት ስቴቶች ትብብር ሲሆን እነርሱም ኢንዲያና፣ ኬንታኪ እና ኦሃዮ ናቸው።
Regional Conferences
The five regional celebrations will be held across North America, including West Coast Zone, Central Zone, Heartland Zone, East Coast Zone and Southern Zone.