Prayer of Jubilee

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሰሜን አሜሪካ
የኢዮቤልዩ ጸሎት መምሪያ

የዓመታት ምስጋና ጸሎት

ሃምሳ ዓመት የአንድ ጎልማሳ ሰው እድሜ ነው! የእግዚአብሔር ታማኝነትና በረከት የተገለጠባቸው ዓመታት ናቸው። እነዚህን ዓመታት ስናስባቸው ተቆጥረው የማያልቁ የእግዚአብሔር ሥራዎች በዚህ በአሜሪካ በተበተነው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውስጥ ታይተዋል። በታላቁ ሰንበት ከበራ የሚሰማን ደስታ የእግዚአብሔርን ፍቅርና መልካምነት የሚያንጸባርቅ እንዲሆን በምስጋና እንጸልይ፡፡ “ቸር ነውና፥ ምህረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ።” (1ዜና 16:34)

አንድነትና እርቅ

እግዚአብሔር በመካከላችን እጅግ ጥልቅና እውነተኛ የሆነ የእርቅና የጸጋ መቀባበል እድል እንዲሰጠን በኅብረታችንም መካከል መከፋፈልን ከሚዘራ ነገር እንድንጠበቅ በክርስቶስ በተገኘም አንድነት ድል እንድናደርግ “10 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ:” 1ቆር 1:10 (ቆሮ. 1:10)

ዝግጅትና አደረጃጀትን በሚመለከት

የሰማይ አባታችን ሆይ! እኛ ይህንን ከፊታችን ያለውን የኢዮቤልዩ በዓል ከበራ ያለአንተ ድጋፍ እንደማናደርገው እናውቃለን፣ ጌታ ሆይ ይህንን ከበራ ልናደርግ ስንዘጋጅ፣ እንያንዳንዱን ተግባርና ክንዋኔም ስንፈጽም ሰማያዊ ምሪትንና የአፈጻጸም፣ ጥበብን ስጠን። “ሥራህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ አሳብህም ትጸናለች።” (ምሳ. 16:3)

የከበራ ተሳትፎን በሚመለከት

የዚህ የኢዮቤልዩ ከበራ፣ ከዝግጅት እስከ አፈጻጸም ድረስ፣ በስምህ ተጠርተው በንጹህ ወንጌል አማኝነት በሰሜን አሜሪካና ከዚያም በላይ ያሉ ክርስቲያን ወገኖች ሁሉ፣ በነቃ ደረጃ የተሳትፎ ሚና እንዲኖራቸው እንጸልያለን! ለያንዳንዱ ሰው የሰጠኸውን የጸጋ ስጦታ ለአካሉ ግንባታ ያውል ዘንድ እንዲያስብ፣ እርስ በርስም እንዲያገለግል፣ ሁሉን ሰው የልብ ዝግጅትና የተግባር ተሳትፎ እንዲኖረው አነሳሳልን። “ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤” (1ጴጥ 4:10)

መንፈሳዊ ተሐድሶ

ክቡር የሆንክ የእግዚአብሔር መንፈስ ሆይ! በዚህ በኢዮቤልዩ ዓመት አቤቱ አድሰን፣ አነቃቃን፣ የልባችንን መንፈሳዊ ነዲድ ዳግም አቀጣጥልልን፣ በፊትህም ህይወታችን እንደነዲድ ተግ ብሎ ይታይልን! “አቤቱ፥ ምሕረትህን አሳየን፥ አቤቱ፥ መድኃኒትህንም ስጠን።” (መዝ 85:7)

ወንጌል ስብከትና ተልእኮ

ይህ የኢዮቤልዩ ከበራ ለቃልህ ታላቅ ታሪካዊ ምልክት ሆኖ እንዲቀር እያንዳንዱን የክንዋኔ መድረከ ሌሎችን በወንጌል የመድረሻ ምክንያት እንድታደርግልን እኛንም የአንተ እጅና እግር እንድንሆን እንድትረዳን በጽኑ እንለምንሃለን። “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ (ማቴ. 28:19)።

ቀጣዩ ትውልድ

የህይወት ለውጥና የመንፈሳዊ መነቃቃት በወጣቶቻችን ዘንድ እንዲኖር በጎ ሐሳብህና ፈቃድህ ነውና ይህ እንዲፈጸም ራሳቸውን ለአንተና ለዚህ ለምስጋናህ ክብር ለምናዘጋጀው የኢዮቤልዩ በዓል በተለየ ሁኔታ እንዲሰጡ ውዳችን ክርስቶስ አንተ በጽድቅ መንገድ እንድትመራቸው እንጸልያለን። እዘዝና አስተምር። በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ፥ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው።” (1ጢሞ 4:12)

የወደፊት እቅዳችን

እኛ ለኅብረታችን አንተ ያለህ የወደፊት እቅድ እጅግ ታላቅ እንደሆነ አናምናለን፣ ስለወደፊቱም የምናቅደው አንተ ቀድመህ እንደምትገኝ በማመን ነው እባክህ አሁንም የኅብረታችን የወደፊት እጣ ፈንታ ብሩህ እንዲሆንልን እርዳን። “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም።” (ኤር 29:11)።

የገንዘብ አቅም

ይህ በዓል የአንተና ስለ አንተ የሚደረግ ነው፣ ለዚህ በዓል ከበረ ያስፈልጋል ተብሎ የሚገመተውና አቅማችን አይመጣጠኑም አንተ ግን ያለመለኪያ ትልቅ ነህ በለጣጋም ነህ! ስለዚህ በአንተ መጋቢነት ታምነናል። እንግዲህ ገንዘብ በሚያስፈልገው ማንኛውም የኢዮቤልዩ ዝግጅት በልግስናህ ጎብኘን! “ነገር ግን ሁሉ አለኝ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ ተሞልቼአለሁ።አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል።” (ፊል 4:19)

ደህንነትና ጥበቃ

ታማኝ እረኛችን አንተ ነህ፣ ከጉዳትና ከመከራም የምትጠብቀን አንተ ነህ፣ በህብረታችን ጥላ ስር ያሉና ለዚህም ከበራ ራሳቸውን እያዘጋጁ ያሉትን ወገኖች፣ በከበራው ወቅት ሆነ በዝግጅታቸው ወቅት፣ በምድር ሆነ በአየር ጥበቃህና ከለላህ ከእነርሱ ጋር ይሁን። ከማንኛውም አደጋና እንቅፋት በጸጋህ ጠብቃቸው። “ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም።” መዝ 121:2-3

በማኅበረሰብ ላይ ተጽእኖ/ ማኅበራዊ አስሚታ

የሰማይ አባት ሆይ! በምንኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ በእኛ ላይ የአንተ ብርሃን ጎልቶ እንዲታይ፣ በዚህም ፍቅርህንና ክብረህን ሌሎች እንዲያዩ፣ ኃይልህንና መለኮታዊ ምሪትህን እንድትሰጠን እንለምንሃለን። በሌሎች ፊት በምንኖረው ኑሮ የሰማይ አባታችንን በእኛ ላይ አይተው ያከብሩት ዘንድ ብርሃንህ በእኛ ላይ ይብራ! “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል።መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” ማቴ 5:14-16

ሰላምና ጽድቅን በሚመለከት

በምንኖርበት ማህበረሰብና በአገረ ኢትዮጵያ በየማኅበረሰቡ የሰላምና የጽድቅ ሥራ እንድንሰራ ራሳችንም እንድንሆንም ትረዳን ዘንድ ጥበብንና ኅይልን እንድትሰጠን እንለምንሃለን፣ “የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።” (ያዕቆብ 3:18)

ለአገልግሎት ራሳችንን ስለመስጠት

እግዚአብሔር ሆይ የአንተ ጸጋና ፍቅር መገለጫ እንሆን ዘንድ የአገልግሎትና ራስን የመስጠት መንፈስ እንዲኖረን፣ በዚህም እንድትባርከን እንለምንሃለን “እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” (ኢያሱ 24:15)

ፍቅር፣ ርኅራሔና ይቅርታ

ጌታ ሆይ በወደድከን ፍቅር ሌሎች የእኛን ፍቅር ሊያገኙ የተገባቸውን እንድንወድ እርዳን፣ ፣በኅብረታችን ውስጥ ባሉን የእርስ በርስ ግንኙነቶች ያለፉ ጉዳቶች እንዲፈወሱ የእርቅና የይቅርታን መንገድ አዘጋጅልን እኛም በድፍረት በዚህ ዓይነት መንገድ መሔድ እንድንችል እርዳን “ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ። ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ። (ቆላ 3:13) ፣ “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። (ዮሐ 13:34)

ለመጭውም ትውልድ

ይህንን የኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ስናከብር፣ ለአብያተ ክርስቲያናት ኅብረትና ለመጭውም ትውልድ የወደፊት ተስፋና ማንሰራራት እንዲሆን የአንተን መተማመኛ እንድትሰጠን እንለምንሃለን። ጽሎታችንም ሆነ ተግባራዊ ጥረታችን አንተንና የአንተን ስም ብቻ የሚያከብር እንዲሆን እንፈልጋለን፣ ስለዚህ ይህንን ኢዮቤልዩም ሆነ የወደፊት እቅዶቻችንን በመጋቢነትህ ፈጽሞውኑ እየተማመንንን፣ ረዴትና ምሪትን እንድናገኝ፣ በእጅህ አደራ አሳልፈን እንሰጣለን “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም” (ኤር 29:11)

መሪዎቻችንን ስለማክበር

ውድ አምላካችንና ዋነኛው መሪያችን ሆይ! በዚህ የኢዮቤልዩ ከበራ ላይ አንተ እኛን እንዲመሩ የወሰንካቸው ሰዎች በዚህ ታሪካዊ ወቅት ተገኝተዋልና እቅዶቻቸውን ሲያስተላልፉ፣ ሲተገብሩ ስራው እጅግ ታላቅ መሆኑን ተገንዝበን አስፈላጊውን ትብብር እንድናደርግላቸው እንድናከብራቸውና እንድንታዘዛቸው ልባችንን ቅን እንድታደርግልን እንለምንሃለን “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ። (እብ 13:17)

ልግስና

አንተ ለደግነህ መለኪያ የሌለህ ቸር አምላክ ነህ፣ ከእጆችህም ያልተቀበልነው አንዳች የለም፣ የዚህ የህብረታችን ሃምሳኛ ዓመት በአል ስናከብር አንተን እግዚአብሔርን በዓላችን አድርገን እንድናከብርህና ዝግጅቶች ሁሉ ገንዘብን በሚመለከት ውጤታማ እንዲሆኑ በደስታ የተሞላ ልግስናችንን እንድንገልጥ የሁላችንን ልብ እንድታነሳሳልን እንጠይቅሃለን “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።” (2 ቆሮ. 9:7)

በጥበብ የተገለጠ መንፈሳዊ እድገት

በምናደርጋቸውና በምንወስናቸው ማንኛውም የኢዮቤልዩ ጉዳዮች ነገሮችን የመለየት ጥበብና አንተን የሚያከብር የብስለት ውሳኔዎችን እንድንወስን በዚህም የኅብረታችን መንፈሳዊ እድገት በጥልቅ እንዲያድግ እንለምናለን፣ “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል።”፣ “ (ያዕ 1:5)፣ “ ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ። ለእርሱ አሁንም እስከ ዘላለምም ቀን ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።” (2 ጴጥ 3:18)

እግዚአብሔርን በመታመን ስለመጽናት

በዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ተግባር ላይ ከሰዎችም ሥርዓት ሆነ ከክፉ ኅይላት እንዲሁም በመካከላችን ሊፈጠር ከሚችል ማንኛውም ዓይነት ተግዳሮት ልናልፍና በድል ወደ ታላቁ አንተን ማክበሪያ ክብረ በዓል ልንደርስ የምንችለው በአንተ በመታመን ስንጸና ስለሆነ እባክህን እምነትንና ጽናትን አብዝተህ ስጠን “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።” (ገላ 6:9)፣ (ምሳሌ 3:5-6)

እግዚአብሔርን ስለ መታመን

እግዚአብሔር ሆይ በሁለ እንተናችን እንታመንህ ዘንድ ረዳታችን ሁነን፣ እኛም በራሳችን ማስተዋል እንዳንደገፍ በሁሉ ነገራችን እግዚአብሔር አንተን ብቻ መታመኛ እንድናደርግህ መንገዳችን ሁሉ ይከናወንልን ዘንድ ለአንተ ሙሉ መገዛትን አስተምረን “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤”(ምሳሌ 3:5-6)

እነዚህን ሁሉ ጸሎቶች

በየስፍራዎች ወደ አንተ ስናደርስ እንደምትሰማን እንደምትመልስልንም አምነናል እንደተቀበልናቸውም በእምነት ቆጥረን የሁሉ የበላይ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናመሰግንሃለን።

ለእያንዳንዱ ጥቅም፣ ለጋራ በረከት፣ ለእግዚአብሔር ክብር ኢዮቤልዩን እናክብር!

THE GRAND JUBILEE CELEBRATION

The event will be held in July 26-27, 2024.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top