Heralding Jubilee!

የኢዮቤልዩ አዋጅ!

እኛ ሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ አምላካችን እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ባለቤት እርሱ ብቻ መሆኑን ያሳውቅ ዘንድ ቀድሞ በደነገገው ኢዮቤልዩ መርህ የሃምሳኛ ዓመታችንን ልዩ በሆነ መልኩ ልናከብር ቆርጠናል! ይህ ኢዮቤልዩ፣ ዋና ዋና የአንቀጹ ሐረጎች በእኛና በሩቅም በሚሰሙን ዘንድ ሁሉ፣ አንድ ካደረገን የክርስቶስ ፍቅር ጋር፣ እንዲገለጥ እናውጃለን! ለእያንዳንዱ ጥቅም፣ ለጋራ በረከት፣ ለእግዚአብሔር ክብር ኢዮቤልዩን እናክብር እንላለን!

የአዋጁ መግቢያ

አዋጅ! አዋጅ! እናንት ወንጌላውያን ስሙ፣ ላልሰማው አሰሙ! እግዚአብሔር ቀድሞ በተናገረበት ቃሉ አሁንም ይናገራልና አድምጡ! ሳቡ ተሰብሰቡ የሰንበታት ሰንበትን ኢዮቤልዩን አስቡ! ታላቁን የጌታን ዓመት ለማክበር በየዞኑ ተሰብሰቡ! ጥንታዌ ጥንቱ፣ አልፋ ኦሜጋው ይጠራሃል፣ ለራስህ ስማ፣ ለቤትህ አሰማ፣ ለማህበሩ አሰማ፣ ኢዮቤልዩ የሰንበታት ሰንበት፣ የታላቅ ተሐድሶ ዋዜማ፣ ጥሪ እነሆ፣ ተጠርተሃል!

በኦሪት ዘሌዋውያን አንቀጽ 25: ንኡስ አንቀጽ 10 እንዲህ ይልሃል፣ “አምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ነው፤ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለስ። ብሏልና እያንዳንድህ ወደ ኢዮቤልዩ ና! ጥሪ ከፈጣሪ ስማ! ላልሰማ አሰማ!

አንቀጽ አንድ – ቅድመ ነገር እርቅና ይቅርታ ይነገር!

የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን እንድታዩ፣ እርሱ እንደሚያያችሁ እርስ በርስ ተያዩ! ይላል፣ ቀዳሚው ኪዳን ይናገራል፣ ይቅር በል፣ ይቅርታን ተቀበል፣ የነከስከውን ልቀቅ፣ አብር ተባበር በክርስቶስ ፍቅር ተሳሰር፣ ሰባራውን ጠግን መንገዱን አድስ፣ እግዚአብሔር ሊጎበኝህ በደጅ ነውና፣ ልቡናህን አጽዳ፣ ታረቅ፣ በበደል ቆጠራ አትራቀቅ፣ ልቀቅ! ልቀቅ! ልቀቅ! እያልን እናውጃለን! አዋጁ የበደል ዕዳ ሰርዝ፣ የቂም እሹሩሩን፣ የጥላቻ መርዙን፣ የክፋት የሸር መዘዙን፣ የበደል መዝገቡን፣ ዝጋው ይልሃል እግዚአብሔር ይህን ይነግርሃል።

አስቀድሞ መሪዎችን ወደ ብርሃን ይጣራል፣ መጋቢዎች፣ ካህኖች፣ ሽማግሌዎች፣ ዲያቆኖች ወንጌላውያን የተልእኮ እንደራሴዎች፣ የቃሉ አገልጋይ መምህራን ሰባኪዎች፣ ዘማሪዎች፣ በየቤትህ በየማህበርህ በዘመድ ወዳጅ መካከል ሰባራውን ጠግን፣ ለእርቅ ተጣራ፣ ፍቅር ያንሰራራ፣ ጸጋና ምህረትን አውጅ ተብለሃል!

አንቀጽ ሁለት – የኅብረት ጸሎትን በሚመለከት

ለጸሎት ተሰብሰብ፣ ትበረታ ዘንድ ስለ አንድነት እንድትጸልይ፣ የሁሉ ድምጽ በአንድነት፣ በምስጋና በምልጃ እንደ እጣን ትመት፣ በጸባኦት በማደሪያው እንዲደርስ፣ ክፉውን አስረህ፣ በፍቅር ተሳስረህ፣ ትውልድን ቤተ ሰብን፣ ማኅበሩን ይዞ ወደ ዙፋኑ በአንድ ልብ በትጋት በፍቅር በታማኝነት ጸሎትህ ይድረስ፣ ጸሎት ሰሚው ጌታ፣ አስቀድሞ “ቀድሳቸው፣ ጠብቃቸው፣ አንድ አርጋቸው” ብሎ የጸለየልህን አስተጋባ ይልሃል! በስደት በኖርክበት ምድር ባርኮሃልና፣ ለምድሪቱ ጸልይ፣ ባርኮትህን ቁጠር፣ ወንጌልን ትሰብክ ዘንድ ተልእኮህን አስብ ይልሃል ንጉሡ!

አንቀጽ ሶስት – ቤተ ሰብን በሚመለከት

በማይሻረው የእግዚአብሔር ቃል፣ የዘመንን ተግዳሮት ተሻጋሪ እንድትሆን፣ ለራስህ ስማ! ቤተ ክርስቲያንን ትውልድ ተሻጋሪ ቤተ ሰብ እንድትሆን ጉልበቷ የሆነውን እግዚአብሔርን ታከብር ዘንድ፣ እንደ ቤተ ሰብ ተሰብሰብ፣ ከቤትህ ያፈገፈግህ ተመለስ፣ ከወዳጅ ከዘመድ ከባልንጀራህ፣ ያፈገፈግህ ተመለስ፣ ባል ከሚስት፣ ሚስት ከባል፣ ልጅ ከወላጅ፣ ወላጅ ከልጅ ያፈገፈግህ ወደ የቤትህ ተመለስ ይልሃል፣ እግዚአብሔር በሰንበታት ሰንበት ይጠራሃል፣ ይህን በማድረግህ ክብሩን በአንተ ሊያበራ፣ መድሃኒትን ለህዝብ በአንተ ሊገልጥ ፈልጓልና ተመለስ ይልሃል!

አንቀጽ አራት – መንፈሳዊ ፈውስና ግለ ተሃድሶን የሚመለከት ጥሪ

የቁስል ጠገግ፣ የስብራት ጠገን እንድታገኝ፣ ወደ መንፈሳዊ ፈውስ፣ ወደ ግለ ህይወታዊ ለውጥ እንድትመጣ ተጠርተሃል፣ በኢዮቤልዩ መንፈስ ታደስ፣ ለዓለም ተስፋ፣ ለጨለማ ብርሃን፣ እንድትሆን፣ የጥሞና የማሰላሰል ጊዜ ውሰድ፣ አረፍ በል! ለእረፍት ተጠርተሃል! “በሕይዎትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይወድቅ ተጠንቀቅ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ፣” ተብለህ በእግዚአብሔር ርኅራሔ የተለመንከውን ቅዱስ መስዋእት አድርገህ ለተሃድሶ ራስህን ወደ መሰዊያው ታቀርብ ዘንድ ስማ!

አንቀጽ አምስት – የድነት ወንጌልንና የሰላም ጥሪን በሚመለከት

የድነትን ወንጌል አዋጅ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጥሪ፣ የመዳን ቀን ዛሬ መሆኑን እንድታውጅ፣ ሰዎች ሁሉ በእምነት የሚድኑበትን የእግዚአብሔር የጸጋውን ወንጌል እንድትናገር፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንደ ሰራዊት በየቀየህ ተደራጅ፣ የምስራቹን ቃል ክርስቶስ ከሞት ተነስቶልሃል ብለህ በዘመቻ እንድታውጅ ተጠርተሃል።

አንቀጽ ስድስት የማኅበር ዝማሬ አምልኮን፣ የሚመለከት

ኅብረ ዝማሬ የአምልኮ ሰራዊት መድብ፣ ድምጸ መረዋ መሳሪያህን ሰብስብ፣ የሚስረቀረቅ  ድምጽ ያላቸውን፣ ባለ ግርማ ሞገስ መዘምራንን፣ በረቀቀ ቅኔ ዝማሬ፣ በጥበብ ቃል ሰብስበህ፣ ኢዮቤልዩን አድምቅ! በልብሰ ዝማሬ በቀለማት ውበት የሰንበቱን ጌታ፣ እንደ በግ ታርዶ እንደ አንበሳ የተነሳውን የትንሣኤ ንጉስ፣ የድነትህን ራስ ክርስቶስን በታላቅ ክብር አንግሥ ይልሃል! ይጠራሃል! የመላእክት ዝማሬን ልታሰማ ተሰብሰብ ይልሃል!

አንቀጽ ሰባት የህዳሴ ጥሪትን ማካፈል በሚመለከት

በላይህ ላይ የክርስቶስ ስም የተጠራብህ ሁሉ ስማ፣ በልዩታ ስጦታ የባረከህ፣ በስራህ በረከት የባረከህ፣ በጸጋው ስጦታ የባረከህ፣ ለመንግስቱ ውበት ብርቅርቅታ፣ በታወጀው ቀን በታወጀው ስፍራ ሁሉን ለአንድነት፣ ለፍቅር ለክብሩ ድምቀት ያለህን ይዘህ ና ይልሃል! በመካከልህ ያሉትን ፈልገው ያጡትን፣ እህል ቢሆን ውሃ፣ የዚህ ምድር ሃብት ማጣት ኑሯቸውን ያከበደባቸውን ታስብ ዘንድ፣ ጥሪትህን እንድታካፍል፣ የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን እንዳደረግችው ታደርግ ዘንድ ደሃውን አስብ፣ የታረዘውን አስብ የተወደደችው የእግዚአብሔር ዓመት እርሷ ናትና ከጎተራህ አውጣ ፣ ለደሃው አምጣ አምላክህ ያደረገልህን ርኅራኄ ትገልጥ ዘንድ ደግነትህን ለሚፈልጉ ግለጥ ይልሃል!

አንቀጽ ስምንት የከበራው መንፈስ እንዲቀጥል ለወደፊት ኪዳን እንትከል

ይህ ከበራ፣ ያለፈውን መዝጊያ የመጪውን መክፈቻ እንደሆነ እወቅ! መጪው ዘመን፣ የአዋጆቹን አንቀጾች እንኖራቸው ዘንድ ጥሪ ቀርቦልናል፣ ብትጋጭ ከቂም ከጥላቻ ተላቀህ ለይቅርታና ለእርቅ ተዘጋጅ፣ የወንጌልን ኅይል በቅዱሳን ህብረት ለመግለጥ ታጠቅ፣  የአዋጁን ቃል ስማ ያለፈውን ከወደፊት ጋር አስማማ መንፈሳዊ ፈውስህ፣ የአንድ ሰሞን እንዳይሆን፣ ለመጪው ስር ነቀል ተሐድሶ ራስህን አስለምድ፣ ኃይለ መለኮትን ከትምህርተ መለኮት ሳታፋታ፣ ለየጉባኤው የሚሆን ንጹሕና ግልጽ ወንጌልን ስበክ፣ በትምህርተ መለኮት ጥናት፣ ለርቱዕ ትምህርት ለወንጌል ጤንነት ትጋ፣ የጋራ ጸሎት፣ በየአካባቢህና በአገር አቀፍ ደረጃ አደራጅ፣ ጊዜው ሳያልፍ የማያልፈውን የወንጌል አገልግሎት ለቀጣይ ትውልድ ልቀቅ፣ ያሳደግናቸው እንዲያሳድጉ፣ የመራናቸው እንዲመሩ ትኪ ቅብብሎሽን አፍጥን፣ የወንጌላውያኑን ኅብረት፣ ከብትንትኖሽ ወደ ግጥምጥሞሽ አምጣ፣ ተሰብሰብ አትበተን፣ ይልሃል፣ እግዚአብሔር በመጪው ሃምሳ ዓመታት እንዲባርክህ የዚህን አዋጅ ጥሪ አንቀጾቹን ፈጽም ተብለሃል።

አንቀጽ ዘጠኝ መደምደሚያና አፈጻጸምን በሚመለከት

ድኅረ ልደተ ክርስቶስ 2023 የበጋው ወራት እንደ ወንጌላውያን በምድሪቱ የተሰበሰብክበት 49ኛ ዓመት ነውና፣ እስከ 2024 የበጋ ወራት ሃምሳኛ ዓመት እንድትቆጥር፣ ወር በገባ የመጀመሪያው ሰንበት ሁልህም በየአጥቢያህ ከነሃሴ 2023 እስከ ሃምሌ 2024 እስከ ታላቁ ሰንበት ኢዮቤልዩ ድረስ ይህንን አዋጅ በየወሩ አውጅ፣ በጸጋው ትምክህት በእምነት የዳንህ፣ የወንጌላውያኑን የእምነት አንቀጽ የተቀበልህ ሁሉ፣ አካል ነህና አባል ነኝ አባል አይደለሁም እንዳትል፣ ነባር ነኝ አዲስ ነኝ እንዳትል፣ ኋላ የፍቅር እዳ፣ ኋላ የእርቅ እዳ እንዳትገባ! ከጎልጎታ አፋፍ ይመለከትሃል፣ ይቅር ያለህ ይቅር በል ይልሃል! ክርስቶስ በችንካሩ ይናገርሃል፣ አዋጅ አዋጅ ስማ ላልሰማው አሰማ! ተብለሃል! በፈረንጁ ዓመት ቆጠራ ከሐምሌ 24 – 27/ 2024 በአሜሪካን ርእሰ ከተማ በዋሽንግተን ዲሲ ስንቅህን ቋጥረህ፣ ካስማህን ወጥረህ ሁልህም አንድ የሚያደርግህ ላይ አተኩረህ ከያለህበት እንድትሰበሰብ የሰንበት ጌታ ክርስቶስ ጠርቶሃል! አዋጅ ደርሶሃል፣ እንዳትቀር ብሎሃል!

ለእያንዳ ጥቅም፣ ለጋራ በረከት፣ ለእግዚአብሔር ክብር ኢዮቤልዩን እናክብር!

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጽሕፈት ቤት ሰሜን አሜሪካ!

THE GRAND JUBILEE CELEBRATION

The event will be held in July 26-27, 2024.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top