የምስጋና ብሥራት!
August 1, 2024
የወርቅ ኢዮቤልዩአችን በታላቅ ደስታና ክብር ተጠናቀቀ!
የአንድነታችን ዓላማና ምክንያት የሆንከው ክርስቶስ ጌታችን ክብር ለስምህ ይሁን!
በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የኀምሳኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ላይ ሁላችሁም በመገኘታችሁ የተሰማን ደስታና ክብር ወደር የለውም!
ይህ በእግዚአብሔር የተባረከ መርሐ ግብር በዋጋ የማይተመን እግዚአብሔር በዘመናት መካከል የሰጠን አስደናቂ መንፈሳዊ “ክስተት” ነው! ከአምላካችን ጋርና እርስ በርሳችን የነበረን ህብረት በቃላት ለመግለጽ አስቸጋሪ እስከሚሆን ድረስ በከፍተኛ ደስታ የተሞላበት ነበር፡፡ ከጁላይ 24 እስከ ጁላይ 27 ድረስ በኅብረታችን ጉዞ የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያየንባቸው 50 ዓመታት የተቋጩባቸውና ለቀጣዮቹ ዓመታት የተዘጋጀንባቸው፣ የታላቅ ከበራ ቀናት ነበሩ፡፡
ረቡዕ ጁላይ 24፣ 10፡00 – 2፡00 ዝግጅቶችን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲመራቸው ለእርሱ አሳልፈን የሰጠንበት ጊዜ ነበር፣ የዚህ ክፍለ ጊዜ ድባብም በመንፈሳዊ ዝግጅትና በመጪዎቹ የከበራ ቀናት እግዚአብሔር በሚያደርገው ባርኮት ናፍቆት የተሞላ ነበር፡፡ ጁላይ 25፣ 9፡00 – 1፡00 እለቱ የጀመረው ከኢትዮጵያና ከቀሩትም አንዳንድ የዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዓለም አቀፋዊ የወንጌላውያን ትብብር እስፈላጊ መሆኑን፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ተሞክሯዊ ውይይቶችን በማድረግ ሲሆን፣ እለቱ የተጠናቀቀው በኅብረቱ የኅምሳ ዓመት ጉዞ አስጀማሪና አስቀጣይ የሆኑትን ግለሰቦች ከታላቅ የራት ግብዣ ጋር እውቅናና ሽልማት በመስጠት ነበር፡፡
ጁላይ 26፣ 9፡00 – 1፡00 በዚህ ቀን የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ከመላው የአሜሪካ ግዛቶች እንዲሁም ከሌሎች አካባቢዎች ሁሉ የተሰባሰቡ የቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ የአገልግሎት ክፍል ኃላፊዎች የተሰባሰቡበትና የቤተ ክርስቲያን ማንነት ከተልእኮ አኳያ፣ በተበታተነ ማህበረሰብ ውስጥ የክርስቲያናዊ አገልግሎት ገጽታ፣ የአዲሱ ትውልድ ተልእኳዊና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች እንዲሁም ለውጤታማ ክርስቲያናዊ ኅብረት የማእከል አስፈላጊነትን በሚገባ የቀረበ ሲሆን ከሰዓት በኋላ ከ1፡00 10፡00 የታላቁ የወር ኢዮቤልዩ ኦፊሲላዊ መክፈቻና ከበራ ነበር፡፡
ጁላይ 27፣ 9፡00 – 1፡00 ሁለት ታላላቅ ክንውኖች በማለዳው ክፍለ ጊዜ በዲሲ ከተማ ተካሒደዋል፣ የወንጌል አዋጅና የእግር ኳስ ግጥሚያ! ከሰዓት በኋላ ከ 1፡00 8፡00 ሁለተኛ ቀን የታላቁ ኢዮቤልዩ ከበራ እጅግ በአስደናቂ ሕብረ ዝማሬና የእግዚአብሔር ቃል እንዲሁም የትውልድ ድምጽን በመስማትና የወደፊት የህብረቱ ዋና ዋና የአቅጣጫ ግንዛቤዎች የቀረቡበትና የጌታን ራት የተካፈልንበት ወቅት ነበር፡፡
በእርግጥም “ለእያንዳንዱ ጥቅም፣ ለጋራ በረከት፣ ለእግዚአብሔር ክብር ኢዮቤልዩን እናክብር!” ያልነው እውን ሆኗል፡፡
በዚህ ታላቅ ታሪካዊ በዓል ላይ የተሳተፋችሁ፣ ከመላው የአሜሪካ ግዛቶች፣ ከካናዳ፣ ከአውሮፓ፣ ከአፍሪካና በተለይም ከኢትዮጵያ እንዲሁም ከሌሎች የዐለማችን አገሮች ለዚሁ ስትሉ በአየር በምድር ተጉዛችሁ የመጣችሁ በመገኘታችሁ ክብር የተሰማን ደስታ ከፍተኛ ነው! ስለ ጸሎቶቻችሁ፣ ስለ አበረታች ቃሎቻችሁና ጥሪአችንን ስለማክበራችሁ እኛ የኅብረቱ መሪዎች በዓለሙ ሁሉ ፊት ልናመሰግናችሁ እንወዳለን፡፡
ይህ አስደናቂ ጊዜ እኛ እንደ አንድ የክርስቶስ አካል ስንሰባሰብ እምነት፣ ተስፋና ፍቅር ያላቸውን ኃይል የመሰከረ ጊዜ ነው! ይህ የኢዮቤልዩ ከበራ ያልለፈውን ታሪክ ማክበሩ ብቻ ሳይሆን የወደፊት ዓላማና ራዕይን በሚመለከት የጫረው ተስፋ ከፍተኛ ነው፡፡
የበዓሉን ማንኛውንም ክንውን በከፍተኛ ባለሙያዎችና ዘመናዊ መሣሪያዎች የተሰነዱ በመሆናቸው ይህንን የዩቲዩብ ሊንክ ሰብስክራይብ በማድረግ ደረጃውን የጠበቀና አግባብ ካለው ምንጭ የቀረቡ ቪዲዮዎችን በማግኘት ተጠቃሚ ይሁኑ! እንዲሁም በፌስቡክ ገጻችን ይከተሉን።
የኢትዮጵያወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጽሕፈት ቤት
Pastor Solomon Telahun
Executive Director, EECFNA
Ethiopian Evangelical Churches Fellowship North America
P.O. Box 13050 Alexandria Virginia, 22312 (EECF), Alexandria, VA 22312 · USA